Matthew 27

ይሁዳ ራሱን ሰቀለ

1ጧት በማለዳ ላይ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስ ስለሚገደልበት ሁኔታ ተመካከሩ፤ 2ካሰሩትም በኋላ ወስደው ለገዥው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።

3አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ተጸጸተ፤ የወሰደውን ሠላሳ ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች መልሶ በመስጠት፣ 4“ንጹሕ ሰው አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ።

እነርሱም፣ “ታዲያ እኛ ምን አገባን፤ የራስህ ጕዳይ ነው!” አሉት።

5ስለዚህ ይሁዳ ብሩን በቤተ መቅደስ ውስጥ ወርውሮ ወጣ፤ ሄዶም ራሱን ሰቅሎ ሞተ።

6የካህናት አለቆች ብሩን አንሥተው፣ “የደም ዋጋ ስለሆነ ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ፤ 7ተመካክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን ቦታ ገዙበት። 8ስለዚህም ያ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተብሎ ይጠራል። 9በዚህም በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ለእርሱ ዋጋ ይሆን ዘንድ የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ሠላሳ ጥሬ ብር ተቀበሉ፤ 10እግዚአብሔርም ባዘዘኝ መሠረት ለሸክላ ሠሪው ቦታ ከፈሉ።”

ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት

27፥11-26 ተጓ ምብ – ማር 15፥2-15፤ ሉቃ 23፥2፡3፡18-25፤ ዮሐ 18፥29–19፥16 11በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው።

ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት።

12የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከስሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም። 13በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከስሱህ አትሰማምን?” አለው። 14እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።

15አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። 16በዚያን ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር። 17ሕዝቡ እንደ ተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ 18ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።

19በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለ ተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት።

20ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር።

21አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ።

እነርሱም፤ “በርባንን!” በማለት መለሱ።

22ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው።

ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ።

23ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጓል?” በማለት ጠየቃቸው።

እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ።

24ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በስተቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ።

25ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ።

26በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

ኢየሱስ በሮማውያን ወታደሮች እጅ

27፥27-31 ተጓ ምብ – ማር 15፥16-20 27ከዚያም የአገረ ገዥው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ። 28ልብሱን ገፍፈው ቀይ ልብስ አጠለቁለት፤ 29እሾኽ ጐንጕነው አክሊል በመሥራት ራሱ ላይ ደፉበት፤ የሸንበቆ በትር በቀኝ እጁ በማስያዝ በፊቱ ተንበርክከው፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት አሾፉበት፤ 30ተፉበትም፤ የሸንበቆ በትሩን ከእጁ ወስደው ራሱ ላይ በሸንበቆው ደግመው ደጋግመው መቱት፤ 31ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፍፈው የራሱን መጐናጸፊያ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።

የኢየሱስ መሰቀል

27፥33-44 ተጓ ምብ – ማር 15፥22-32፤ ሉቃ 23፥33-43፤ ዮሐ 19፥17-24 32ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። 33ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣ 34ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም። 35ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤
ጥቂት የጥንት ቅጆች “በነቢዩ ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ የተባለው ይፈጸም ዘንድ” የሚል አላቸው።
36በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣ 37“ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ። 38ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው አብረውት ተሰቅለው ነበር። 39መንገድ ዐላፊዎችም በኀይል እየተሳደቡና ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ 40“ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን ውስጥ የምትሠራው፤ እስቲ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ በል ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር።

41የካህናት አለቆችም ከኦሪት ሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እያሾፉበት እንዲህ ይሉ ነበር፤ 42“ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። 43በእግዚአብሔር ታምኗል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስቲ ከወደደው አሁን ያድነው!” 44ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

የኢየሱስ መሞት

27፥45-56 ተጓ ምብ – ማር 15፥33-41፤ ሉቃ 23፥44-49 45ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 46በዘጠኝ ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

47በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ጩኸቱን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን እየተጣራ ነው!” አሉ።

48ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጦ ሰፍነግ በመውሰድ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ነከረው፤ ሰፍነጉንም በሸንበቆ ዘንግ ጫፍ ላይ በማድረግ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት። 49የቀሩት ግን፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያድነው እናያለን!” አሉ።

50ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ።

51በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤ 52መቃብሮች ተከፈቱ፤ አንቀላፍተው የነበሩትም ብዙዎች ቅዱሳን ተነሡ፤ 53ከመቃብርም በመውጣት ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ወደ ቅድስት ከተማ ገብተው ለብዙዎች ታዩ።

54የመቶ አለቃውና አብረውት ኢየሱስን ይጠብቁት የነበሩት የመሬት መናወጡንና የሆነውን ነገር ሁሉ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው፤ ይህስ፣ “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አሉ። 55ከገሊላ የመጡና ኢየሱስን በሚያስፈልገው ነገር ለማገልገል የተከተሉት ብዙ ሴቶች ሁኔታውን ከርቀት እየተመለከቱ በአካባቢው ነበሩ። 56ከእነርሱም መካከል ማርያም መግደላዊት፣ ማርያም የያዕቆብና የዮሴፍ እናት እንዲሁም የዘብዴዎስ ልጆች እናት ነበሩ።

የኢየሱስ መቀበር

27፥57-61 ተጓ ምብ – ማር 15፥42-47፤ ሉቃ 23፥50-56፤ ዮሐ 19፥38-42 57ምሽት ላይ ዮሴፍ የሚባል ሀብታም ሰው ከአርማትያስ መጣ፤ እርሱ ራሱም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ። 58ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስን በድን ለመነው፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። 59ዮሴፍም በድኑን ወስዶ በንጹሕ የበፍታ ጨርቅ ከፈነው፤ 60ለራሱ ከዐለት አስፈልፍሎ ባዘጋጀው መቃብር ውስጥ አኖረው፤ ከዚያም ትልቅ ድንጋይ አንከባልሎ የመቃብሩን በር ዘግቶ ሄደ። 61በዚህ ጊዜ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም ከመቃብሩ ትይዩ ተቀምጠው ነበር።

የመቃብሩ ጥበቃ

62በማግስቱም፣ ከሰንበት ዝግጅት በኋላ ባለው ቀን፣ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ጲላጦስ ፊት ቀርበው እንዲህ አሉት፤ 63“ክቡር ሆይ፤ ያ አሳች በሕይወት ሳለ፣ ‘ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ’ ያለው ትዝ ብሎናል፤ 64ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን ሰርቀው ለሕዝቡ፣ ‘ከሙታን ተነሥቷል’ ብለው እንዳያስወሩ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ ትእዛዝ ስጥልን፤ አለዚያ የኋለኛው ስሕተት ከፊተኛው የባሰ ይሆናል!”

65ጲላጦስም፣ “ጠባቂዎች አሏችሁ፤ ሄዳችሁ በምታውቁት መንገድ አስጠብቁ” አላቸው። 66እነርሱም ሄደው መቃብሩን በማኅተም አሽገው ጠባቂ አቆሙበት።

Copyright information for AmhNASV